ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 03 ቀን ፣ 2018 ዓ.ም ፣ “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጲያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጲያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
ሠንደቅ ዓላማ “የአንድ ሀገር መንግሥትና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ ነፃነት፣ ዕድገትና ማሕበረሰባዊ ትስስር መፍጠሪያ መሣሪያ ነው፡፡
ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የታተመ የሀገራዊ አንድነትና ነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው፡፡ የአንድነታችንና የሕብረታችን ማሳያ፣ ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪዎችን አሸንፈው ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ የሕይዎት መስዋዕትን ከፍለው ለአዲሱ ትውልድ አስረክበዋል፡፡
ይህንኑ መሠረት በማድረግ ሠንደቅ ዓላማ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት የሚከበር ታላቅ ሀገራዊ በዓል ነው፡፡
በመሆኑም የሀገራችንን ሠንደቅ ዓላማ ክብርና ተገቢውን ከፍታ አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሀገራዊ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን ማስቀጠል፤ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት በማጽናት የሀገራችንን የዕድገት ከፍታ ማረጋገጥ ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ነው፡፡
የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሠንደቅ ዓላማ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 863/2006 (እንደተሻሻለው) አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ መጀመሪያ ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጓል፡፡
የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በተለያየ መልኩ በየዓመቱ እየተከበረ አስራ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ዓመትም “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጲያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጲያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታን በዋጀ መልኩ ለ18ኛ ጊዜ የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 3 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ፣ በፌዴራል፣ በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ከተሞች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦና የኢትጵያን ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራትና ማንሰራራት በሚያረጋግጡ ውይይቶች ታጅቦ በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሪነት በመላው አገሪቱ ይከበራል፡፡
የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል መከበሩ ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን በማስጠበቅ የኢትጵያን የከፍታ ብሥራትና ሕዳሴ ለማረጋገጥ ለሀገር ክብርና ጥቅም ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በሠንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃሉን የሚያድስበት ዕለት ይሆናል፡፡
በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሠንደቅ ዓላማ በመስቀልና በሠንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ የመፈፀም ሥነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ይሆናል፡፡

