August 26, 2025
Africa Amharic

አንድ ድርጅት እንዴት የፓርቲ መሪና የፓርቲ ሊቀ መንበር ይኖረዋል?

                      ክፍል 2

የ #ኢዜማ የአደረጃጀት መርህ በሀገርና በድርጅት ፍላጎትና ጥቅም መሀከል ሊኖር የሚገባውን ጤናማ ግኙነት ከማረጋገጥ አንጻር፤

በሀገራችን በተለይ በምርጫ ስም ሥልጣን መያዝ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ በአሸናፊነት እራሳቸውን ያስቀመጡ ድርጅቶች በሀገርና ሕዝብ ላይ ካደረሱት ከፍተኛ ጉዳቶች መሀከል አንዱ የድርጅትን ፍላጎትና ጥቅም ከሀገር ፍላጎትና ጥቅም ለይቶ ካለማየት የደረሰው ጉዳት ነው።

የመጀመሪያው የጉዳት ዓይነት በማናቸውም በተረጋጉ ሀገሮች የሚታየውን መንግሥትን ሳይሆን ሀገርን እንደ ሀገር የሚያስቀጥሉ ተቋማት ፈጽመው እንዳይፈጠሩ ያደረገው ጉዳት ነው። ይህ ሁኔታ በምርጫ በሥልጣን ላይ የፈለገው ዓይነት ድርጅት ይምጣ የአሸናፊውን ድርጅት ፖሊሲዎች የሚተገብር በየጊዜው እያደገና የበለጠ ውጤታማ እየሆነ የሚሄድ የሲቪል ሰርቪስ አካል ሀገሪቷ እንዳይኖራት አደርጓል። የዚህ ጉዳት ውጤት ወደፊት በትክክለኛ ምርጫ ሥልጣን ላይ ለሚመጡ እንደ ኢዜማ ላሉ ድርጅቶች ከፍተኛ ፈተና መሆኑ የሚቀር አይደለም።

እስካሁን ያለው ሁኔታ የሚያሳየው በተለያዩ መንግሥታዊ መሠረታዊ ተቋማት፣ እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ መለከላከያ፣ ደኅንነት፣ የፍትሕ አካላት ያሉ መሥሪያ ቤቶች ያላቸው ዝግጅት የተለያዩ ፖሊሲዎችን ለማስተናገድ የሚችል አይደለም። በመዋቅር፣ በአሠራርና በሰው ምደባ ደረጃ ያላቸው ዝግጅት የአንድ የፖለቲካ አመለካከትን ታማኝነት መመዘኛ ያደረገ ነው። በመሆኑም ከሌላ የፖለቲካ አመለካከት የሚነሳ ፖሊሲዎችን ይዞ የሚመጣ ድርጅት የእነዚህን ቁልፍ ተቋማት መዋቅር፣ አሠራርና የሰው ምደባ ከመሠረቱ እንዲለውጥ ያስገድደዋል። ለዚህ ለውጥ የሚወጣው የሀገርና የሕዝብ ሀብት እንኳን እንደ ሀገራችን ያለች ደሀ ሀገር ቀርቶ አቅም ባላቸውም ሀገራት የሚቻል አይደልም። ይሄም ብቻ አይደለም፣ እስካሁን በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ እነዚህ ድርጅቶች ሀገራዊ ይዘትና አቋም እንዳይኖራቸው ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይቃወሙኛል የሚላቸውን ኃይሎች ማፈኛ ሲያደርጋቸው ኖሯል።

በኢዜማ እምነት፣ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም የግድ የሀገርና የድርጅት ፍላጎቶችንና ጥቅሞች ባወቀና በለየ መልኩ መሥራት የሚያስችለው የአወቃቀርና የአሠራር ባህል ያለው ድርጅት ያስፈልጋል።

ለዚህም ነው ኢዜማ፣ ሀገራዊና መንግሥታዊ ጉዳዮችን ከድርጅታዊ ጉዳዮች ለይቶ ዝግጅት ማድረግ የሚያስችል የመዋቅርና የአሠራር መርህ የተከተለውና ተግባራዊ እያደረገ ያለው።

ሁለተኛው ጉዳት፣ በሀገር፣ መንግሥትና በድርጅት መሀከል ሊኖርው የሚገባው ልዩነት በአግባቡ አለመለየቱ የመንግሥትን ሀብትና ንብረት ለድርጅት ጥቅምና ፍላጎት እንዲውል ያደረገው ሁኔታ ነው። ይህ ሁኔታ በሥልጣን ላይ ያለውን ድርጅት አላግባብ የሕዝብን ሀብትና ንብረት ለድርጅት ጥቅምና ፍላጎት በማዋል በቀጥታ ያደረሰው ጉዳት ነው።

በሌላ በኩል በሥልጣን ላይ ያለው ድርጅት በከፍተኛ ደረጃ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በሚያደርገው ፉክክር እጅግ አድሏዊ የመፎካከሪያ አቅም ሰጥቶታል። ይህ ሁኔታ በሀገራችን የሚደረጉ ምርጫዎች ሚዛናዊና ፍትሀዊ እንዳይሆኑ በማድረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዳይገነባ ከፍተኛ ችግር የሆነ ጉዳይ ነው።

ለዚህም ነው ኢዜማ፣ የሀገርንና የመንግሥትን ንብረት ለድርጅት ጥቅም አለመዋሉን የሚያረጋግጥ የመዋቅርና የአሠራር መርህ የተከተለውና ተግባራዊ እያደረገ ያለው።

ምስል: ዮሐንስ መኮንን (የኢዜማ ም/መሪ)
ማዕረጉ ግርማ (የኢዜማ ም/ ሊቀመንበር)

Source: EZEMA

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *