
አዲስ አበባ
ሐምሌ 29 .2017ዓ.ም /ኦገስት 5. 2025 ዓ.ም
እንደሚታወቀው የሶማሌ ክልል በተለያዩ ግዜያቶች የተለያዩ ፈታኝ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ያሳለፈ ክልል ሲሆን፤ እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የክልሉን ማህበረሰብ ህልዉናና የአኗኗር ዘይቤን በቀጥታ ተፅዕኖ ያሳደረና ለፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የዘፈቀ ሁኔታዎች እንደነበሩ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የተፈጠሩት በተለያዩ ግዜያቶች ክልሉን የመሩት የክልሉ የፖለቲካ ልሂቃንና አስተዳደሮች በሚያደርሷቸው ግድያ፣አፈናና፣እንግልት እና ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያቶች የክልሉና የክልሉ ማህበረሰብ የጉዳቱ ሰለባ ሊሆን ችለዋል፡፡ ይሁንና የአካባቢው ማህበረሰብ እነዚህን ከባድና አስቸጋሪ ከግዜ ወደ ግዜ እየተንከባለሉ የመጡ ሁኔታዎችን በትዕግሥትና በብልሐት ሊያሳልፍ የቻለ ሲሆን ለዚህም አቅም የሆነው ማህበረሰቡ የሰነቀው ተስፋና የለውጥ ራዕይ ምክኒያት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ከላይ ከጠቀስናቸው በተጨማሪ የሶማሌ ክልል ከመጀመሪያ እንደ ክልል ከተቋቋመበት እለት ጀምሮ እስካሁን በትክክል የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ በህዝቡ የተመረጠ መንግስትና ፍላጎቱን የሚያንፀባርቅ እውነተኛ ውክልና አላገኘም፡፡በተቃራኒው ክልሉ የህዝብ ባልተመረጡና ባልተወከሉ አስተዳደሮች ምክንያት የተበላሸ አስተዳደር ስርዓት፣የፍትህ መጓደል፣በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ግጭት፣ ኋላ ቀርነት ሙስናና ብልሹ አሰራር እና ሌሎች በደሎች ገፈት ቀማሽ ሆኖ አሳልፏል፡፡ በየግዜው ሲፈጠሩ የነበሩ ለውጦችም የማህበረሰቡን ጥያቄ እንመልሳለን በሚል በቃላት ሽንገላ የተከሸነ ብቻ ሆኖ በመቀረቱ ማህበረሰቡ በየግዜው እናገኝ ይሆን የሚሉትን መልስ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነባቸው መጥቷል፡፡
የሶማሌ ክልል ቀደምት ስርዓቶችን ስናጤን በክልሉ ውስጥ የነበረውን መጠነ ሰፊ ጭቆና አስተዳደራዊ በደሎችን ላለመቀበል የሚሹ የማህበረሰቡ የለውጥ ማዕበሎች ነበሩ፡፡ እነዚያን ስርአቶች ለማሸነፍ ብዙ ጥረትና ተጋድሎዎችን በማድረግ ምንም እንኳን በየግዜው ቢከሽፉም ለውጦችን ያመጡ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ሁሌም የተሻለና ትክክለኛ ለውጥ ይመጣል በሚል ጽናት በማድረግ ማህበረሰቡ በየግዜው በሚከሰቱ የስርዓት ለውጥ ተስፋ ቢሰንቁም ቃል የሚገቡት አስተዳደሮች የመሪነት ሚናን ሲቆናጠቱ ለውጡን በመቀልበስና የገቡትን ቃል በመዘንጋት ማህበረሰቡን ከማገልገልና የህዝቡን ጥያቅ በሂደት ከመመለስ እንደቀደምቶቹ ሁሉ የለውጡ መሪዎች ከበፊቱ በከፋ መንገድ ሰብዓዊ ጥሰቱንም፣ ፍትህ ማጓደሉንም፣ ዘረፋውንም፣ ሌብነቱንም፣ ሙስናውን፣ ግድያና እስሩንም አፈናና እንግልቱንም ቀጥለውበታል፡፡ይህም የክልሉ ማህበረሰብ አብዝቶ እንዲጮህ ምክንያት ሆኖታል፡፡
አሁን በስልጣን ላይ የሚገነው የክልሉ አስተዳደር በዚህ ሂደት የተፈጠረ ተስፋ የተጣለበትና እውነተኛ ለውጥ ያመጣል ብለን ተስፋ የጣልንበት የነበረ ቢሆንም ከበፊቶቹ ሁሉ የከፋና ከፋፋይ አስተዳደር ሊሆን ችሏል፡፡ይህንን ለውጥ እንዳይከሽፍና እንዳይቀለበስ በየግዜው ከአስተዳሩ ጎን በመሆንና ድጋፍ በማድረግ የማህበረሰቡ የቆዩ የፍትህ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እንዲመልስ በየግዜውና በተለያዩ ግዜያቶች ብንጠይቅም አሻፈረኝ በማለት በከፍተኛ ሁኔታና ከበፊቶቹ በከፋ መልኩ በደልና ጭቆናን እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ ይህም ስለሆነ እኛ የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ ምሁራንና የማህበረሰብ ተወካዮች አሁን በሙሰጠፌ መሀመድ ኡመር የሚመራው የክልሉ መንግስት አስተዳደር ግዜ እንዲያበቃና በሌሎች ህዝባዊ ቅቡልነት ባላቸው ተወካይ እንዲተካ የወሰነው፡፡ስለሆነም ዛሬ ነሐሴ 29 2017 ዓ.ም እኛ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች የሚከተሉትን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
- የሀገሪቱ እና የክልሉን ብሎም የአከባቢውን ሰላምና መረጋጋት እንዲጠበቅና በክልሉ ውስጥና በአጎራባች አካባቢው የሚገኙ ወንድም ህዝቦች መካከል ሰላማዊ አብሮ መኖርን ሁኔታ እንዲጠናከር።
- በብልጽግና ፓርቲ የተጀመረውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደት እንዲጠናከርና በጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የተቀረጸውን ፍትሃዊ ሀገራዊ የብልጽግና እድገት ተጠቃሚነት በክልሉ እንዲተገበር።
- በፌደራል መንግስት ጥረት እየተደረገበት የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚነት በተለይ በክልላች የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ የማውጣት ሂደት የምንደግፍ መሆኑን እናሳውቃለን።
- በክልሉ ም/ር ቤት የፀደቀው አዲሱ የክልሉ መዋቅር ጥናትና ውይይት ያልተደረገበት በመሆኑና ግጭትና የሰላም ማደፍረስ የሚያስከትል በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆምና እንዲታገድ።
- በአቶ ሙስጠፌ መሀመድ ኡመር የሚመራው የክልሉ አስተዳደር ለውጡን ማስቀጠል ባለመቻሉና በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማለትም ፣ የፍትህ እጦት፣ ግጭት፣ መፈናቀል፣ አፈናና እስር እንግልት፣ ሙስና ለብነትን እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ በማንሰራፋቱና ይህንን የተቃወሙ አካላትን በማሰርና በማሳደድ ምክንያት በመሆኑ በአስቸካይ መንግስታዊ ስልጣኑን እንዲለቅ እንጠይቃለን፡፡
- በክልሉ የምትገኙ ሙሁራን፣የማህበረሰብ ተወካዮች፣ ወጣቶችና ማህበረሰብ አንቂዎች ትግሉን እንድትቀላቀሉና የሙስጠፌ አመራር ከቦታው እንዲነሳ የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንድትደግፉና እንድትሳተፉ እንጠይቃለን፡፡
- የክልሉ መንግስት የክልሉን ለውጥ መምራትና ማስቀጠል ባለመቻሉ የፌደራል መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ከግምት በማስገባት በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ፡፡
- የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሊከሰት ዳዳር እያለ ያለውን አጎራባች የሚገኙት የክልል ህዝቦችና ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ግጭቶች መፍትሔ እንዲሰጥ፡፡
- በመጨረሻም የፌደራል መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚደግፈው ከሶማሌ ህዝብና ፣ ፖለቲካዊ ክስረት ካጋጠመው ከክልሉ አስተዳደር አንዱን እንዲመርጥ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ከ11 የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች ይህንን የአቋም መግለጫ ተሳታፊ ወሆናቸውን ነቢርማቸው አረጋግጠዋል፡፡
ሰላም ለሀገራችን ጤና፣ እድገትና ብልጽግና ለህዝባችን
ሐምሌ 29 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ
#Office_of_the_Prime_Minister-Ethiopia
#Abiy_Ahmed_Ali
#Prosperity_Party – ብልፅግና