
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የካቲት 11 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገራችንን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የነበረውን ታሪካዊ ቀዳሚነት፣ አሁን ካለው ፈጣን የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር በማቀናጀት አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ይህ እምርታ ተቋሙን በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ አድርጎ የሚያስጠራ ስትራቴጂካዊ ድል ነው።
90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ባከበረበት በዚህ ወቅት፣ አየር ኃይሉ የታሪክ ኩራት ብቻ ሳይሆን የዘመናዊነት ተምሳሌት መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።
የአየር ኃይላችንን አሁናዊ ቁመና ልዩ የሚያደርገው ዋና ነጥብ የሌሎችን እጅ ከመጠበቅ ተላቆ ራሱን መቻሉ ነው። ተቋሙ በገነባቸው ከባድና ቀላል የጥገና ማዕከላት አማካኝነት፦ ተዋጊ የጦር ጄቶችን፣ የትራንስፖርትና የውጊያ ሄሊኮፕተሮችን፤ የተለያዩ የማሰልጠኛ አውሮፕላኖችን የመጠገን፣ የማሻሻልና የማዘመን ሙሉ አቅም ፈጥሯል።
ይህ ስኬት ሃገራችን ልታወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከመቆጠቡም በላይ፣ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግርን በተግባር ያረጋገጠ ታላቅ ብሔራዊ ድል ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም የጥራትና የብቃት መለኪያውን ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጓል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቅርብ ጊዜ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ የሱ-30 ባለ ብዙ ሚና ተዋጊ ጄቶችን በመታጠቅ፣ የአየር ላይ የመምታት አቅሙን በማይደፈር የልዕልና ደረጃ ላይ አድርሷል።
እነዚህ ጄቶች በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታና የአየር ንብረት ውስጥ ተልዕኮን የመወጣት ልዩ ብቃት ያላቸው የቴክኖሎጂ ጥበቦች ናቸው።
ይህም ዘመናዊ አደረጃጀት አየር ኃይሉ የነገ የሰማይ ላይ ጀግኖችን በላቀ ዲሲፕሊንና በረቀቀ ቴክኖሎጂ ለማፍራት ያስቻለው የጥራት መሠረት ሆኗል።
የታጠቃቸው ቴክኖሎጂዎች ጠላትን ከሩቅ ርቀት የመለየትና እንቅስቃሴውን በንቃት የመከታተል አቅም ያለው በመሆኑ፣ ለአየር ኃይላችን የማይተኛ የሰማይ ላይ አይን ሆኖ ያገለግላል።
የዘመኑ የአየር ላይ ውጊያ ከበረራና ከፍንዳታ ባለፈ፣ በረቀቀ የኤሌክትሮኒክስ ፍልሚያ ላይ የተመሰረተ ነው። አየር ኃይላችን በዚህ ረገድ ያለውን ቁመና በማፈርጠምና የጠላትን የቴክኖሎጂ የበላይነትና የጥቃት ዝግጅት አስቀድሞ በማምከን፣ የጦርነቱን የኃይል ሚዛን ወደ ወገን የመመለስ ልዩ አቅም ፈጥሯል።
በተጨማሪም አየር ኃይል ዘመናዊ መሣሪያ ያለ ዕውቀት ፋይዳው አነስተኛ ነው የሚለውን መርህ በመከተል፣ የሪፎርሙ ልብ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ አርፏል።
በዚህም አብራሪዎችን፣ የጥገና መሐንዲሶችንና የቴክኒክ ባለሙያዎችን በከፍተኛ ጥራት በማሰልጠን የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
በሌላ በኩልም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ሰፋፊ የውጊያና የሎጂስቲክስ መሠረተ-ልማቶች፣ ተቋሙ ፈጣን ተንቀሳቃሽነትን (Mobility) በተግባር እንዲያረጋግጥ አስችለውታል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ የጀግንነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት የመራመድ፣ የመታደስና የቴክኖሎጂ ባለቤት የመሆን ታሪክም ጭምር ነው። ትናንት በአፍሪካ ቀዳሚ ነበርን፤ ዛሬ ደግሞ በዘመናዊነት ዳግም ከፍ ብለናል።
ይህ የተቋሙ አዲስ ቁመና በ90ኛው የምስረታ በዓል ላይ በክብር እንግድነት በተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም አንደርሰን እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች እና በሌሎች እንግዶች ፊት በጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ደምቆ በኩራት የታየ እውነታ ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በጽኑ የሚያስከብር፣ በአስተማማኝ ቁመና ላይ የሚገኝ “የሰማይ ላይ ጋሻ” አላት። ከአየር ኃይል የሰራዊት ስነ ልቦና ግንባታ ዳይሬክቶሬት

