ታላቁ ዐሊም ህልፈታቸው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የሽኝት ስነስርዐቱ እና ሌሎች ተጠባቂ መርሃግብሮች የሁላችንም አባት የሀገር ምልክት የሆኑትን ዐሊም ክብራቸውን እንዲሁም እስላማዊ አደቡ ተጠብቆ እንዲፈፀም በተለያየ መንገድ አስተዋፅኦ የነበራቸውን አካላት እንደሚያመሰግን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገልጿል ።
በተለይም ለኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ፣ለሰላም ሚኒስቴር ፣ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር፣ለአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ፥ለሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ለፌደራል ፓሊስ ፣ለአዲስ አበባ ፓሊስ፣ ለኦሮሚያ ፓሊስ፣ ለአዲስ አበባና ለፌደራል ትራፌክ ፓሊስ ፣ለደንብ ማስከበር ለቀብር አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ፣ለኑር መስጂድ እና ለአንዋር መስጂድ ወጣቶች፣ ለመንግስት እና ግል መገናኛ ብዙሃን ፣ለመላው የከተማችን ነዋሪዎች በሙሉ የታላቁ አሊም የክቡር ዶ/ር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ የቀብር ስነስርአት በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጋችሁት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ትልቅ ክብር ያለው መሆኑን እየገለፀ ምስጋናውን ያቀርባል ብሏል ።
ታላቁ ዐሊም የሁሉም ኢትዮጵያውያን አባት እንደመሆናቸው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላሳየው ፍቅርና ክብር ጠቅላይ ምክርቤቱ ትልቅ ክብር እንዳለው አስታውቋል ።
የሀይማኖት ተቋማትም ህዝበ ሙስሊሙ ተወዳጁን አባት እና አሊም ባጣበት ፣ ከጎኑ በመቆም ሀዘኑን ለመካፈል ያደረጉት ሁሉ ታሪክ የማይረሳው እንደሆነ ባስተላለፈው መልዕክት ገልጿል ።

