September 21, 2025
Africa Amharic News

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አቤ ሳኖ የሚመራ የባንኩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጅዳና አካባቢው ከሚኖሩ ዳያስፖራ ጋር ውይይት አደረጉ

የባንኩ የልዕውካን ቡድን በጅዳና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ በማስተላለፍ እና ባንኩ በሚሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶችና ማበረታቻዎች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ ክቡር አቶ አቤ እንደገለጹት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው መሰረታዊ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ፖሊሲ ለውጥ በኋላ ወደ አገር ቤት እየገባ ያለው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ ቢሄድም በህጋዊ መንገድ የሚገባው አነስተኛ በመሆኑ ላኪ ዜጎችም ሆኑ አገሪቱ ከውጭ ምንዛሬው በሚገባ መጠቀም አለመቻላቸውን በመግለጽ ይህ ሁኔታ ብዙዎችን፣ በተለይም በቤት ሠራተኛነትና በሌሎች ስራዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎችን ለችግር እንደዳረገ አስታውሰዋል።

ህገ ወጥ ተግባሩን ለመከላከል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተዘጋጁ አመቺ አማራጮች ዜጎች ቢጠቀሙ ራሳቸውን ከችግር ተከላክለው ለአገርም በዉጭ ምንዛሬ አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚያስችላቸው አብራርተዋል።

የባንካችን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ኑሪ ሁሴን በውይይት በድረኩ ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር የሃዋላ መላኪያ፣ የቁጠባ ሁኔታና ዝቅተኛ ወለድ፥ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር እና ሌሎች ከባንኩ አገልግሎት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመድረኩ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በሳኡዲ አረቢያ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ሙክታር ከድር የባንኩ ፕሬዝዳንትና የልዑካን ቡድናቸው ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ከፍተኛ ቁጥር ለያዘው በሳኡዲ ዓረቢያ ለሚገኘው ዳያስፖራ የባንኩን አገልግሎት ማስተዋወቃቸው መንግስት ለዜጎች የሰጠውን ትኩረት የሚያመለክት መሆኑን አስታውሰው ባንኩ በዚህ ረገድ ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመጨረሻም ክብር ፕረዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ሳውዲ አረቢያ ጂዳ እና ሪያድ ከተማ የተካሄዱት የውይይት መድረኮች ውጤታማና ብዙ ተሞክሮ የተወሰደባቸው እንደነበሩ ገልጸው በቀጣይነት የዲያስፖራ ዜጎችን ቀልጣፋና የተሳለጠ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ በርካታ ስራዋች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *