September 21, 2025
Africa Amharic Ethiopia News

በሕይወት እያለሁ የግድቡን መጠናቀቅ የማየት ህልሜ እውን በመሆኑ ደስተኛ ነኝ”

መሐመድ አልአሩሲ

በሕይወት እያለሁ የግድቡን መጠናቀቅ የማየት ህልሜ እውን በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ሲሉ መሐመድ አልአሩሲ ተናገሩ።

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጥብቅና በመቆም በአረብኛ ሲሟገቱ የሚታወቁት እና የምክር ቤት አባል የሆኑት ብሎም የውሀና ኢነርጂ ሚንስቴር አማካሪ መሐመድ አልአሩሲ ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የዓባይ ግድብ ተጠናቆ ማየት ትልቁ ሕልማቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች በተባበረ ክንድ አድዋ ላይ የጥቁሮች ኩራት የሆነውን ደማቅ ድል የተቀዳጀች ሀገር እንደመሆኗ መጠን ሕዳሴውንም አጠናቅቃ ሪቫን ለመቁረጥ በመዘጋጀቷ ደስተኛ ነኝ ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቁጭት የጀመረችውን የሕዳሴ ግድብ በራሷ ፋይናንስ ምንጭነት ታሪክ በመስራቷ ዳግማዊ የዓድዋ ድል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሐብቷ እንዳትጠቀም ብዙ ዘመቻዎች ሲደረጉ እንደነበር የገለፁት አቶ መሐመድ፤ በሁሉም መስክ ቁርጠኝነቷን በመሳየት የባንዳዎችን ምኞት ከንቱ ማድረግ እንደቻለች ጠቁመዋል።

የውጪና የውስጥ ጫናን በመቋቋም ግድቡን ለመመረቅ ጥቂት ቀናት የቀሯት ኢትዮጵያ ቀድሞውንም የሌሎች የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን ጥቅም የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በይፋ ስትገለፅ መቆየቷን አንስተዋል።

በዚሁ መሰረት የተፋሰሱ ሀገራት ብዥታ እንዲስተካከል የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ስራ እንዲሁም በአረብኛ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ በመሟገትና ገለፃ በማድረግ ለምርቃት መብቃታችን ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

የድል ብስራቱን ቀን ለማዬት ትልቅ ጉጉት ነበረኝ ያሉት አቶ መሐመድ፤ በሕይዎት እያለሁ በማየቴ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሳይሰስቱ ግድቡ የእኔ ነው በማለት ያላቸውን አበርክተው የአንድነት አሻራቸውን አሳርፈው ደማቅ ድል ስላሰመዘገቡ ደስታቸው የላቀ መሆኑን በመግለጽ፤ በዚህም ኢትዮጵያ አሸንፋለች ሲሉ ገልጸዋል።

ይህን ደማቅ ድል በባሕር በርም መድገም ግድ ነው ያሉት አቶ መሐመድ፤ እሳቸውም በማንኛውም የኢትዮጵያ ከፍታ ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን የአገራችንን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ የተለመደው አብሮነታችንን ማስቀጠል አለብን ሲሉ አሳስበዋል።

በዋስሁን ተክሌ
++++++++++++++++++

Gazette Plus ጋዜጣ ፕላስ

ጋዜጣ_ፕላስ #ኢትዮጵያ #ዓባይ #አባይ #ህዳሴ #ግድብ

ግብጽ #መሐመድ_አልአሩሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *