በመጪዎቹ የዻጉሜ እና የመስከረም ወራት በመዲናችን አዲስ አበባ ለሚካሄዱት የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት, ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ , ሁለተኛው የካረቢያን እና አፍሪካ መሪዎች“ካሪኮም” ጉባኤን አስመልክቶ ከሆቴል ኢንዱስትሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ላይ ጠቃሚ ዉይይት አድረገናል ።
የአገራት መሪዎችን ፣ የአለም አቀፍ ተቋማት ፣ የአየር ንብረት ተመራማሪዎችን ፣ አለም አቀፍ የሚዲያ አካላትን ጨምሮ ከ 25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የአየር ንብረት ጉባኤ በመዲናችን መካሄዱ ባለፉት የለዉጥ አመታት ለዘርፉ ልማት የሰጠነዉን ከፍተኛ ትኩረት ተገቢነት የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ናቸዉ ።
መዲናችን አዲስ አበባም ከዚህ ቀደም ከተለመዱ ዉስን ጉባኤዎች በእጥፍ የላቁ አለም አቀፍ ኩነቶችን በስኬት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች ፣ ለአብነት በተጠናቀቀዉ የበጀት አመት 150 አለም አቀፍ ኩነቶችን በከፍተኛ ስኬት ያስተናገደች ሲሆን 1.3 ሚሊዮን ያህል ጎብኚዎችንም አስተናግዳለች በዚህም 143 ቢሊዮን ብር ያህል ሀብት ወደ ኢኮኖሚያችን ገቢ ሆኗል ።
ለዚህ ከፍተኛ ዉጤት መመዝገብ አዲስ የተገነቡ ፣ የታደሱ ነባር የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች፣ የከተማችን ነዋሪዎች የእንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት ፣ የግሉ ዘርፍ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመንግስት የተናበበ ቅንጅት ፣ ጉልህ ድርሻ አላቸዉ።
ጉባኤዎቹ የመዲናችንን አዲስ ገፅታ ፣አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ረገድ የሚኖራቸዉ አስተዋፆ ጉልህ በመሆኑ ይህንን ግብ ለማሳካት በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜትና የላቀ የአምባሳደርነት ሚና ይበልጥ ተቀናጅተን መስራታችን እንዲቀጥል ጥሪዬ አቀርባለሁ ።