
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2017 ( Horncurrent.com ) የሁለተኛው ዙር ኮሪደር ልማት አካል የሆነው ከ4 ኪሎ እስከ እንጦጦ ኮሪደር ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ባለፈ በጥራትና በፍጥነት አጠናቆ ለሚፈለገው ዓላማ ማዋል ከመቼውም ጊዜ በላይ ባህላችን እየሆነ መምጣቱ ዛሬ ያስመረቅናቸው ከ4 ኪሎ እስክ እንጦጦ ኮሪደር እውነተኛ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ዘመናዊ የሀገር ግንባታ ሂደት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ተቋማት መገኛ፣ የህዝብ እንደራሴዎች መቀመጫ፣ የምሁራን አምባ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መገኛ፣ በሀገሪቱ የመጀመሪያው የህክምና ተቋም የካቲት 12 ዘመናዊ ሆስፒታል መገኛ፣ የመጀመሪያው የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ሙዚየሞች፤ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማትና እንዲሁም የከተማችን የእደ ጥበብ ውጤቶች ልህቀት ማዕከል የሆነው ሽሮሜዳ መገኛ በአጠቃላይ በርካታ ግዙፍ መንግስታዊና ታሪካዊ ተቋማት የሚገኙበት መስመር የሚሸፍነው እና 314 ሄክታር ስፋት ያለው መሬት በኮሪደሩ መልማቱን ገልጸዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ በፊት የነበረው 32 ሜትር የመንገድ ስፋት ወደ 42 ሜትር መስፋቱን፣ 3 ሜትር የብስከሌት መንገድ እንዲሁም 11 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 11 የታክሲ እና የአውቶቡስ መጫኛና ማውረጃዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም 20 አረንጓዴ ቦታዎችና 2 ፕላዛዎች፣ 10 የህጻናት መጫወቻ፣ 7 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ጨምሮ 9 መጸዳጃ ቤቶች፣ ከ5 እስከ 13 ሜትር ስፋት ያለው 11 ነጥብ 4 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ፣ 2 (1 ዘመናዊ ሞልን ያካተተ በመንግስትና የግል አጋርነት እየተገነባ ያለ ተርሚናሎች እና 11 የታክሲ/ባስ መጫኛና ማውረጃዎች ያሉት እንዲሁም 7 የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች እና 417 ስማርት ፖሎችን ያካተተ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ይህንን መስመር መልሶ ማልማት፣ ማደሰና ማስዋብ ለሀገራችንና ለህዝባችን ታሪክ ያለንን ክብር የሚገልፅ ከመሆኑም በተጨማሪ ከ15 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በፊት የነበሩት 751 ሱቆች ሲሆኑ በአዲስ የተሰሩ 770 ሱቆችን በመጨመር 1 ሺህ 521 ሱቆች በኮሪደሩ የኢኮኖሚ ልማት እና የንግድ ልውውጥ እንዲያድግ መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ከንቲባዋ ለፕሮጀክቶች ስኬትና በዚህ ደረጃ ዕውን መሆን ለደከሙ እንዲሁም በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
Source: Fana Broadcasting Corporate S.C.