አሶሳ፤ ሐምሌ 19/2017 በክልሉ የሕዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች የመመለሱን ተግባር ለማጠናከር የገቢ አቅምን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በከሰዓት ውሎው ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የ2017 በጀት ዓመት ሪፖርት ዙሪያ የምክር ቤት አባላት ጥያቄ እና አስተያየት አቅርበዋል።
የምክር ቤቱ አባላት የመንገድ፣ የጤና እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑባቸውን አካባቢዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ምን ታስቧል የሚሉም እንዲሁ።
ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ከምክር ቤቱ አባላት በተነሱ ጥያቄዎች ላይ በሰጡት ምላሽ፤ የሁሉንም ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ክልሉ የራሱን ወጪ በራሱ አቅም መሸፈን አለበት ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 5 ቢሊዮን ብር እንደተሰበሰበ ተመልክቷል።
ይህም ሆኖ የገቢ አቅምን አሟጦ መጠቀም እና ዘመናዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት መከተል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ክልሉ ካለው የገቢ አቅም አንፃር አሁንም ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ገልጸው፤ ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የክልሉን የገቢ አቅም ጥናት ላይ ተመስርቶ መፍትሄ ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።
የክልሉ የገቢ አቅም ከተሻሻለ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙም ጨምረው ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባላትም የተጠናከረ ገቢ አሰባሰብ ስርዓት እንዲኖር በክትትልና ቁጥጥር ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም አገልግሎትን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጋር ተከታታይ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
Source: Ethiopian_News_Agency