
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2017 , የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ህጻናት ያለባቸውን የማንበብ እና የመረዳት ችግር እ.አ.አ በ2035 ለማስቀረት በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
በአፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ዘመን የህጻናት መሰረታዊ የማንበብ፣ የመጻፍ እና የሂሳብ ክህሎቶችን ማላቅ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ከፍተኛ የባለድርሻ አካላት አውደ ጥናት ሐምሌ 15 እና 16 ቀን 2017 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
አውደ ጥናቱ በአፍሪካ 10 ዓመት የሞላቸው ህጻናት የማንበብ እና የመረዳት ችግርን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የበለጠ ማፋጠን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራል።
በሁነቱ ከ25 የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የተውጣጡ የቴክኒክ ተወካዮች፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ተመራማሪዎች እና የልማት አጋሮች ይገኛሉ።
አውደ ጥናቱ አፍሪካ ህብረት እየተገበረ ያለው የትምህርት ስትራቴጂ ትግበራ አካል እንደሆነ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
ስትራቴጂው ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የህጻናትን መሰረታዊ የማንበብ፣ የመጻፍ፣ የመረዳት፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ክህሎቶችን ማዳበር ይገኝበታል።
የባለድርሻ አካላት ምክክሩ በአፍሪካ የህጻናት የትምህርት እና ክህሎት ልማት ላይ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎች እና ፈተናዎችን በመምከር የመፍትሄ ሀሳቦችን ያቀርባል።
ውጤታማ ተሞክሮዎችን ከብሄራዊ የትምህርት ፖሊሲዎች ጋር ማቀናጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
አውደ ጥናቱ አፍሪካ ህብረት እ.አ.አ በ2035 የህጻናትን የማንበብ እና የመጻፍ ችግር የማስቀረት ቁርጠኝነት አካል እንደሆነም ገልጿል።
ራዕዩ የህብረቱ አባል ሀገራት የትምህርት እና ክህሎት ልማትን ለማጠናከር ቃል የገቡበት ናውክቾት ድንጋጌ እና የአፍሪካ ህብረት የ10 ዓመት የትምህርት ኢኒሼቲቭ (2025–2034) በግልጽ መመላከቱን ጠቅሷል።
አህጉራዊው ምክክር የሚደረግባት ኢትዮጵያ ህጻናትን በቀዳማይ ልጅነት ዘመናቸው መሰረታዊ የማንበብ እና የመጻፍ ክህሎቶች እንዲያዳብሩ ባከናወነቻቸው ስራዎች አመርቂ ውጤቶችን አግኝታለች።
የትምህርት ሚኒስቴር ህጻናት በቀዳማይ ልጅነት ትምህርት ወቅት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የማድረግ ተግባርን ለአብነት ይጠቀሳል።
የመምህራንን የስልጠና ጥራት የሚያሻሽሉ ፕሮግራሞችን የማጠናከር እና አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራምን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ማዕቀፎችንም ተግብሯል።
ጥረቶቹ በኢትዮጵያ የማንበብ እና መጻፍ አለመቻል ምጣኔን በታችኛው የትምህርት እርከን እንዲቀንስ ማድረጉና በገጠሪቱ ክፍል የታየው ለውጥ አበረታች የሚባል እንደሆነም ተመላክቷል።
Source: Ethiopian_News_Agency