August 3, 2025
Africa Amharic Ethiopia News

3ኛው የአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

አዲስ አበባ: ሀምሌ 14/2017ዓ.ም “Empowering Africa through trade and Investment Synergies” በሚል መሪ ቃል 3ኛው የአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል እየተካሄደ ነው።

ጉባኤውን የከፈቱት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አብዱልሃኪም ሙሉ(ዶ/ር) የአፍሪካ ሀገራት አብሮ የማደግና የመበልፀግ የረዥም ጊዜ ህልማቸውን የሚያሳኩት በተናጥል ጉዞ ሳይሆን ድንበር ዘለል የሆነ በሀገራት ፣ በተቋማትና በህዝቦች መካከል ትስስርንና ትብብርን በመፍጠር እንደሆነ አንስተዋል።

አያይዘውም በአፍሪካ አገራት የሚደረግ የኢንቨስትመንት ሚና በአህጉሪቱ ያለውን የኢንዱስትሪ እምቅ አቅም በመጠቀም፣ ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በማስፋፋት ለዜጎች የስራ እድል መፍጠርና የገበያ ትስስርን በማጎልበት ለእድገት አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሆነ ገልፀዋል።

ጉባኤው በአፍሪካ ሀገራት መካከልና አፍሪካ ከሌሎች ሀገራት ጋር ስትራቴጂክ አጋርነትንና ትብብርን ለማጠናከር፣ አዳዲስ የገበያና የፋይናንስ እድሎችን ለመፍጠር፣ድንበር ተሻጋሪ ንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ እና በየአካባቢው ያሉ የገበያ እድሎችን ለማሳየትና በዘርፉ የአፍሪካን እምቅ አቅም ለማሳየትና የአፍሪካን ገፅታ አጉልቶ ለማሳየት ያለመ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ጉባኤውን ያዘጋጀው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ሴንተር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲሆን በጉባኤው ከአፍሪካና ከሌሎች አገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የኢንዱስት ሀላፊዎችና ባለሃብቶች እንዲሁም አህጉርና አለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች የጉባኤው ተሳታፊዎች ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *