
ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም፤ ) በዛሬው እለት በክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ሰብሳቢነት፣ ክቡር አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌን ጨምሮ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀላፊዎች የተሳተፉበት ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን፣ ለኤምባሲያችን የበጐ አገልግሎት ተልእኮ ተሰጥቷል፡፡
በክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጭነት ካለፉት አመታት ጀምሮ እየተከናወነ ባለው የክረምት በጎ አድራጎት መርሃ ግብር መሠረት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዘንድሮው የክረምት በጐ ፈቃድ አገልግሎት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በድሬዳዋ ከተማ ለሚኖሩ አቅመ ደካማ ዜጐች 10 ቤቶችን መገንባት ነው፡፡ ይህንን በጐ ተግባር በናይሮቢ የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ የሚሲዮኑን ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች፣ ዳያስፖራውን እንዲሁም ወዳጆችን በማስተባበር ለማከናወን እድሉን አግኝቷል፡፡
የግንባታ ሥራው በኬንያ የኘሮፌሽናል ኢትዮጵያውያን ማህበር አባል እና በቅርቡ ወደ አገር ቤት በመግባት የቴክኖሎጂ ሽግግር ባደረገው ከእንቁ የዳያስፖራ አባላት መካከል አንዱ ከሆነው አቶ ቅዱስ አስፋው ጋር በመተባበር ነው፡፡
አቶ ቅዱስ አስፋው የወዳደቁ ፕላስቲኮችን እና ተረፈ ምርቶችን ወደ ሕንጻ ግንባታ መሣሪያ የሚቀይር ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማራ ኪቡክ የተባለ ድርጅትን የመሰረቱ ሲሆን፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የአካባቢ ጥበቃን ለማጐልበት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዓይነት ላይ የተሰማራ ነው፡፡
በኬንያ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያ እና ወዳጆች፣ እንዲሁም የሚሲዮኑ ዲኘሎማቶችና ሠራተኞች፤ ሁሌም ለአገራቸሁ ጥሪ ፈጣንና አዎንታዊ ምላሽ የምትሰጡ በመሆናችሁ፤ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች፤ በዚህም ልትኮሩ ይገባል፡፡ በተመሣሣይ ሚሲዮኑ ለዚህ ታሪካዊ በጐ ተግባር እድሉን በማግኘታችን እንኳን ደስ አለን ለማለት ይወዳል፡፡
ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ይህንን መልካም ተግባር እንድናከናውን እድሉን ስለሰጡን ሚሲዮኑ ታላቅ ምስጋናውን እያቀረበ፤ ስራውን አጠናቀን እንደምናስረክብ ባለ ሙሉ ተስፋ ነን፡፡